Tuesday, December 3, 2013

የመለስ ዜናዊ አስገራሚ ቃለ-ምልልስ ሲዳሰስ እስክንድር ነጋ

ጠ/ሚ/ሩ ቃለምልልስ እየሰጡ ነው… ቅዳሜ መጋቢት 3/2ዐዐ3 …በዚያን ሰሞን ሞላ ብሎ የነበረው ሰውነታቸው አሁን ከሳ ብሏል… ውይ! ውይ! ውይ!… እኔን! ግን… ግን… ከትላንት ወዲያ ቱኒዚያ፣ ትላንት ግብፅ፣ ዛሬ ደግሞ ሊቢያ እየተፈራረቁባቸው ከሳ ማለትማ ይነሳቸው እንዴ?… «ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል» እንጂ፣ የሰሞኑ የመለስ የስጋት ኑሮ «ውስጡን ለቄስ» እንደተባለው ነው… የስቃይ ኑሮ… አሳዛኝ ኑሮ… እኔን!
የወትሮው «መፈክር አውራጁ» መለስ ዛሬ ቀዝቀዝ ብለዋል፡፡ ስለኢኮኖሚው ተጠይቀው ሲመልሱ ሃሳባቸው ሌላ ቦታ ይመስላል፡፡ ዋናዎቹን ጥያቄዎች እየጠበቁ ይመስላሉ… የቱን ጥያቄዎች?… ከእንጥፍጣፊዎቹ በኋላ የሚመጡትን… ህዝባዊ ተቃውሞ በኢትዮጵያ ይቀሰቀሳል ብለው አልሰጉም ወይ? (ያው መስጋታቸው ቢታወቅም…) ህዝባዊ ተቃውሞ ቢነሳ፣ ሠራዊቱ እንዲተኩስ ትዕዛዝ ይሰጣሉ ወይ?… የግብፅና የቱኒዚያ ሠራዊቶች በህዝባቸው ላይ አንተኩስም ማለታቸውን እንዴት ይመለከቱታል?… ህዝባዊ ተቃውሞ ቢነሳ፣ ሥልጣንዎን በፈቃድዎ ይለቃሉ ወይ?… አውራው የዴሞክራሲ እንቅፋት መለስ ዜናዊ ናቸው የሚባለውን እንዴት ይመለከቱታል?… ኧረ ስንቱ ! ኧረ ስንቱ !… እነዚህ ጋዜጠኞች አንጀታችንን ሊያርሱት ነው… ሶፋዬ ላይ ተመቻቸኹ… ዛሬ ጉድ ሊፈላ ነው!!
እንጥፍጣፊ ጥያቄዎቹ ግዜ እየፈጁ ነው… ሃ… ሃ… ሃ… ሃ… ሃ… አዘጋኹ… አሰልቺ ጥያቄዎች፣ አሰልቺ መልሶች… በእጄ የያዝኹትን መፅሃፍ ማገላበጥ ጀመርኹ… ደቂቃዎች አለፉ…
ሴቷ ጋዜጠኛ ጀመረችው… ደስ አይልም?… ወንዶቹ ደግሞ ይቀጥላሉ… አለሳልሳ ነው ጥያቄውን ያቀረበችው… እነዚህ ጋዜጠኞች ተነጋግረው መሆን አለበት… ቀስ ብለው ጀምረው፣ ሳይታሰብ ሊያፍረጠርጡት መሆን አለበት…
«በሰሜን አፍሪካ ሕዝባዊ ተቃውሞ ያስነሱት ክስተቶች በኢትዮጵያ ውስጥም እንዳሉ ተቃዋሚዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ላይ እርስዎ ምን አስተያየት አለዎት?»… አለቻቸው ጋዜጠኛዋ… በጨዋ ቋንቋ የቀረበ ቆንጆ ጥያቄ… በጨዋ ቋንቋ ለሚቀርቡ ከበድ ከበድ ለሚሉ ጥያቄዎች ጥሩ በር ከፋች….
መለስ ዜናዊ ምላሽ እየሰጧት ነው…
«እኔ ተመሳሳይ ተቃውሞ ይነሳል የሚል ግምት የለኝም…» …እያሉ ነው መለስ፤ የሚጠበቅ ነው… «ለምን ይነሳል?…» …እየተሟሟቁ ነው ጠ/ሚ/ራችን… «ህዝቡ የ5 ዓመታት ኮንትራት ከሰጠን ገና 1ዐ ወራት እንኳን በደንብ አላስቆጠሩም…» …እሺ አቶ መለስ፤ ቀስ ይበሉ…
«በድምፁ፣ በካርዱ ነው ይሄን ኮንትራት የሰጠን…» …ሳላውቀው ሶፋው ጠርዝ ላይ ደርሻለኹ፤ ምንም ነገር እንዳታመልጠኝ እየተለጠጥኹ ነው… «ለመፈፀም ቃል የገባነውን ዳር ለማድረስ ጠዋት ማታ ደፋ ቀና እያልን ባለንበት ግዜ፣ አሥር ወር ሳይሞላ በመንገድ ላይ ነውጥ ሊያስቆመን የሚወጣው ለምንድን ነው?…» …አልበቃዎትም አቶ መለስ?… «በዚያ ላይ ደግሞ…» …ቀጠሉ ጠ/ሚ/ሩ… «ኢትዮጵያ በህግና በሥርዓት፣ በሰላማዊ መንገድ መንግሥት ለመለወጥ የሚቻልበት ሀገር ናት…» …አሁን ጆሮዬን እየኮረኮርኹ ነው… የማዳምጠው በትክክል ነው?… «ከ5 ዓመታት በኋላ ህዝቡ ምርጫ ካርዱን ተጠቅሞ ኢሕአዴግን በዝረራ ከሥልጣን ሊያባርረው እንደሚችል ህዝቡ ያውቀዋል…» …አሁን ከተቀመጥኹበት ፍንጥር ብዬ ተነስቻለሁ!… ህዝቡ ያውቀዋል? ነው ያሉት?… አቤት!… አቤት!… አቤት!… አቤት አለማፈር!… «ኢሕአዴግም ያውቀዋል…» …አሉ መለስ …ባለቤቴ ሳቋን ለቀቀችው… «ይሄን እያወቀ ለምንድን ነው ወደ መንገድ ላይ ነውጥ የሚሄደው?» …እዚህ ጋር መለስ ተሽከርካሪ ወንበራቸውን ትንሽ ወደኋላ ገፋ አደረጉት… እና… እና… ሁለቱንም እጃቸውን አወናጨፉ!… ለካ በስሜት ከንፈዋል… አይ መለስ!
ቃለ-ምልልሱ አበቃ… ጠ/ሚ/ሩ ተነስተው ወጡ…
ታዲያ፣ ለዚህ ምን ምላሽ ነው የሚሰጠው? የት ነው የሚጀመረው? ወደ ሰኔ 1983 እንመለስ? ሁለት አስርት ዓመታት ወደኋላ ተጉዘን፣ ሰፊ ህዝባዊ መሠረት በነበረው ኢዴኃቅ ላይ የሽግግር መንግሥቱ አካል አንዳይሆን በር በመዝጋት የተጀመረው ኢ-ዴሞክሲያዊነት፣ ዘንድሮ ወደ ተዘመገበው 99.6% «የምርጫ ድል» እንዴት እንዳደገ እንዘክር? «ዝክረ ኢ-ዲሞክራሲ ወኢሕአዴግ» ልንለው እንችላለን፡፡ አንድ ትልቅ መፅሃፍ ይወጣዋል፡፡
እዚህ ውስጥ መነከር ግን፣ ወይ የጠ/ሚ/ሩን አባባል እውነት ነው ብሎ የሚያስብ አንድ ሰው ሊኖር ይችላል ብሎ መጠራጠርን ይጠይቃል፣ ወይ ደግሞ፣ ሌላ የሚፃፍለት ቁምነገር ጠፍቶ፣ አንድ ሺህ ግዜ ስለተፃፈለት እውነታ ለአንድ ሺህ አንደኛ ግዜ መፃፍ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ፣ መለዕኮታዊ ትዕግሥትና የተትረፈረፈ ግዜ ያስፈልገዋል፡፡ በእኔ በኩል ሁለቱም የለኝም፡፡
ስለዚህ፣ በአዲሱ ሚሊኒየም በአስገራሚነቱ ቀዳሚ ስፍራ የያዘውን ምላሻቸውን በትዝብትነቱ ብቻ በማስቀመጥ አልፌዋለኹ፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ትንሽ ሳልዳስሰው የማላልፈው ጉዳይ ግን አለ፡፡ ከመለስ አስገራሚ «ትንታኔ» ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሰፊ ባሕር ነው፤ በጥልቀት ልሄድበት አልከጅልም፡፡
ቅድመ 66 አብዮት፣ የቤተመንግሥት ስርዓት ነበር፡፡ ይህ ሰፊ አድማስ ያለው ወግ፣ በተራዘመ አዝጋሚ የለውጥ ሂደት (ፈረንጆቹ Evolutionary የሚሉት) ዳብሯል፡፡ ርዕሰ ብሔርነቱንና መንግሥትነቱን አቀናጅተው ለሺህ ዓመታት የዘለቁት የኢትዮጵያ ነገስታትና መኳንቶቻቸው ከአቋቋም፣ ከአቀማመጥ፣ ከአነጋገር፣ ከአለባበስና ከአበላል አንስቶ እስከ ኃይማኖት፣ ግልቢያ፣ ውጊያና ፍርድ አሰጣጥ ድረስ ተምረዋል፡፡ ታላላቆቹ ነገሥታት በአንዱ ወይም በሌላው የላቀ ብቃት አስመዝግበዋል፡፡ ብዙዎቹ በመንፈሳዊነታቸውና በተዋጊነታቸው ልቀው ወጥተዋል፡፡ የአንዳንዶቹ የገዘፈ ክህሎት በታሪክ ማሕደር ላይ ጎላ ብሎ ሰፍሯል – - – አፄ ዘርያዕቆብ በመንፈሳዊነታቸው፣ አፄ አምደፅዮን በወታደራዊ አመራር ሰጪነታቸው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ነገሥታቱ ሀገር ከመጠበቅና ከመምራት ባሻገር፣ ለሚመሩት ሕዝብ አርአያ ሆኖ መመሰል ይጠበቅባቸዋል፡፡ አበላላቸው፣ አቀማመጣቸው፣ አነጋገራቸው ወዘተ… ጭንቅ ውስጥ የገባው በዚህ ታሳቢ ነበር፡፡
ይህ ግን ለመለስ ዜናዊ ቦታ እንደሌለው ትላንት አብስረውልናል፡፡ «በጠ/ሚ/ርነቴ ኮንትራት የገባሁት ለ8 ሰዓታት ስራ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪRole Model (አርአያ) ለመሆን የገባሁት ውል የለም፡፡ የታመመን በመጠየቅ፣ ትምህርት ቤት በመመረቅ አላምንም» ብለው እቅጩን ነግረውናል፡፡ (ቀጥተኛ ጥቅስ ነው፡፡)
በመለስ ቀመር፣ ከአነጋገራቸው ጋር «ኮንትራት» የለንም፡፡ የእኛ «ኮንትራት» ኢኮኖሚው በምን ያህል አደገ? የዋጋ ግሽበቱ በቁጥጥር ስር ውሏል ወይ? የውጭ ንግድና የመንግሥት ባጀት ጉድለቶች ምን ደረጃ ላይ ናቸው? በሚሉትና በመሳሰሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ብቻ የታጠረ ነው፡፡
ስለዚህም፣ መለስ ዜናዊ እንዳመጣላቸው እየተናገሩ ይኸው ሃያ ዓመታትን አብረን አዝግመናል፡፡ በዘፈቀደ የሚወረውሯቸውን ቃላትና አባባሎች እያደመጠ የተኮተኮተ፣ ያደገና ለአቅመአዳም የደረሰ አንድ ትውልድ በቅሏል ማለት ነው፡፡
ይህ ትውልድ ለእውነትና ለጨዋነት ምን ያህል ዋጋ ይሰጣል? የሚለው ጥያቄ ሁልጊዜ ያሳስበኛል፡፡ መለስ ዜናዊ ተገነዘቡትም አልተገነዘቡትም፣ መሪዎች በሁሉም ሀገራት ትልቁን የአርአያነት ሚና ይጫወታሉ፤ በጥንቷ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ አሜሪካዊያን፣ ፕሬዝዳንቶቻቸው ስለትናንሽ የግል ሕይወታቸው ሳይቀር እውነት መናገራቸውና አለመናገራቸው ከልብ የሚያስጨንቃቸው ተቀናጥተው አይደለም፡፡ ለውሸቱ ዋጋ የማይከፍል መሪ፣ መዋሸትን እንደ ነውር የማይቆጥር ትውልድ ያፈራል ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ የእነሱ ስጋት በሀገሬ እውን ሆኖ እንዳላይ የምር እፈራለሁ፤ እድሜ ለመለስ፡፡
ከዚህ ባሻገር፣ ከጠ/ሚ/ሩ የቅዳሜ ጠዋት ቃለምልልስ የሚገኘው ቁም ነገር፤ ጋዳፊ ባለፈው ሰሞን ሰጥተውት ከነበረው ቃለምልልስ ጋር መመሳሰሉ ነው፡፡ ሕዝባቸው ሆ! ብሎ ለዴሞክራሲ ስለመነሳቱ የተጠየቁት ጋዳፊ፣ «የአልቃይዳ ሴራ ነው» ብለው ዓለምን ማስደመማቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
የእኛው አቶ መለስ ደግሞ፣ «ሕዝባዊ ተቃውሞ የሚነሳ ከሆነ፣ ከበስተጀርባቸው ሻዕቢያ አለበት» ብለው ከወዲሁ ነግረውናል፡፡ እንደ ጋዳፊ እስከሚፈነዳ አልጠበቁም፤ ፈጣኑ መሪያችን!! «አዲስ አበባን በፈንጂ አናውጦ እንደ ባግዳድ ማድረግ የተሳነው ሻዕቢያ፣ በመንገድ ላይ ነውጥ ባግዳድ ሊያደርጋት ምሏል» ብለው አርድተውናል፡፡
በሌላ አነጋገር፣ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲው ጥያቄ ምንጭ ሕዝቡ ሳይሆን ሻዕቢያ ነው ማለታቸው ነው፡፡ ሕዝቡማ «በምርጫ ካርዱ ኢሕአዴግን ከስልጣን ሊያባርረው እንደሚችል ያውቃል» ብለውናል እኮ ጠ/ሚ/ሩ፤ ቀደም ብለው፡፡ እንደ ቱኒዚያ፣ ግብፅ እና ሊቢያ ጎዳና ላይ የሚወጣ ካለ፣ ወይ የሻዕቢያ ሴራ አስፈፃሚ ወይ ሰለባ ከመሆን አያልፍም፤ ለሃያ ዓመታት «ደግመን ደጋግመን በምርጫ ካርዳችን ኮንትራት እንደሰጠናቸው ጠ/ሚ/ራችን» ገለፃ ከሆነ፡፡
ጋዳፊ የቀበጣጠሩት የሞትና የሽረት ትንቅንቅ ላይ ሆነው ነበር፡፡ ድንግርግራቸው በቂ ምክንያት ነበረው፡፡ ለመከላከል እንኳን ፋታ ባጡበት ቅፅበት ነው ከአልቃይዳ ጀርባ ለመደበቅ የተተራመሱት፡፡ በአባባላቸው ዓለም አልተገረመም፤ ሳቀባቸው እንጂ፡፡
መለስ በአካል ምንም አይድረስባቸው እንጂ፣ በመንፈስ ከጋዳፊ የተሻለ ቦታ ላይ አይደሉም፡፡ ተጨንቀዋል፣ ተጠበዋል፡፡ የአእምሮ እረፍት የሚባል ነገር ከራቃቸው ውለው አድረዋል፡፡ «ዛሬ ነገ የጎዳና ላይ ተቃውሞ ቢነሳ ብለን እንቅልፍ ሳይወስደን አናድርም» ብለው ከትንሽ ደቂቃዎች በፊት የፎከሩት መለስ ዜናዊ፣ የሻዕቢያን ስም ያለቦታው ሲያነሱ የተጨነቀው ገፅታቸው ፍንትው ብሎ ለመታየት በቅቷል፡፡
ሻዕቢያን ሙጥኝ ያስባላቸው ጭንቅ ነው፡፡ አይገርምም፤ ያስቃል እንጂ፡፡
ለመለስም ሆነ ለጋዳፊ፣ ከጭንቅ መገላገያው ዘይቤ በጣም ቀላል ነው፡፡ ድፍረትን፣ ቅንነትንና ጀግንነትን ግን ይጠይቃል፡፡
ስልጣንን በፈቃደኝነት መልቀቅ!!!
አሁኑኑ!!!
ምን እየጠበቁ ነው?
ፀሃፊውን ለማግኘት serk27@gmail.com
SOURCE ABUGIDA

No comments:

Post a Comment