ነፃነት ዘለቀ (አዲስ አበባ)
ለለውጥ ያህል ከራሴ ችግር ብጀምር ምን አለበት? ግለሰብ ካልኖረ ማኅበረስብ አይኖርም፡፡ ደሞም የኔ ችግር የሁሉም ፣
የሁሉም ችግር የኔ መሆኑን የማያምን አንባቢ ቢኖር ችግር አለበት ማለት ነውና በጊዜ ራሱን ፈትሾ መድሓኒት ቢጤ
ቢያፈላልግ ሳይሻለው አይቀርም፡፡
ትንሹዋ ወያኔ ጠምሳኛለች፡፡ እኔን ብቻም አይደለም የጠመሰችው፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንንም እንጂ ነው፡፡ ከወያኔ
ባልተናነሰ ሁኔታ ኑሯችንን እያቃወሰችው ትገኛለች – ትልቁ ወያኔ በደጅና በቤት ውስጥ እርሷ ደግሞ በቤት ውስጥ ብቻ
በተናጠልና በቡድን እየተጋገዙ ወዲያ ወዲህ ውልፊት ልንል በማይቻለን ሁኔታ ወጥረውናል፡፡ ምን እንደምናደርግም
ጨንቆናአለ፡፡ ይቺ የቤት ውስጥ ወያኔ ዐይጥ ናት፡፡
ዘመኑ ለይቶለት የዐይጦችና የወያኔዎች ሆኗል ወንድሞቼና እህቶቼ ማለትም ኢትዮጵያውያን፡፡ በኔ ቤት የተረፋት ነገር
የለም፤ ለወትሮው ካልሲና ጨርቃ ጨርቅ እየለቃቀመች ነበር ወደጎሬዋ እምትወስድ፡፡ ዛሬ ግን ዘመን ተቀይሮ ባዶ
ሞሰብ ሣይቀር መቆርጠም፣ አልሙኒየም የምጣድ አከንባሎ መጎርደም፣ ቁም ሣጥን መቀርጠፍ ይዛለች፤ ወያኔነት ከዚህ
በላይ አለ? መጽሐፎችን አንብባ ላታነብ ነገር በጥርሶቿ መከታተፍ፣ ምግቦችን ከጉሮሮዋችን እየነጠቀች ማንከት፣
በሌሊትና አንዳንዴ ደግሞ በማንአለብኝነትና ወደር በሌለው ዕብሪት በቀንም ቤትን ተቆጣጥራ ሰላምን ማወክ የዘመናችን
ትንሹዋ ወያኔ ገደቡን ያለፈ የድፍረት ተግባር ሊሆን በቅቷል – ወያኔን ተማምና መሆን አለበት መቼም፡፡ ድፍረቷ እኮ
ድፍረት እንዳይመስላችሁ፡፡ ኧረረረረረ…. እንዳቃጠልሽኝ የሚያቃጥል ይዘዝብሽ፡፡ ብዙ ሰዎች በርሷ እንደተቸገሩና
ዘመኑ ለርሷና ለወያኔ ዓይነቶቹ ምሥጥ መሠሪዎች የሰጠ መሆኑን ይህን ችግር የማወያያቸው ሰዎች ሁሉ ይነግሩኛል፡፡
ዛሬና አሁን በኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 6፡30 ገደማ ሲሆን ቀን የገዛሁትን እንትን በስምንት የጦር
ግምባር አጥምጄ ወደብሶት አደባባይ መውጣቴ ነው – እንዳትሰማኝና እንዳታውቅብኝ ነው የገዛሁትን ነገር በእንትን
የገለጸኩላችሁ ታዲያን – እንጂ “እዚያው በላች እዚያው ቀረች” የሚል አደገኛ መርዝ መግዛቴን ለመናገር አፍሬ
እንዳይመስላችሁ፡፡ ለነገሩ ወያኔና ዐይጥ ከጠላታቸው የሚከላከሉበት ብዙ ተለዋዋጭ ዘዴ ስላላቸው በበሶ ዱዔት
ያዘጋጀሁትን ግብዣ እንደሚቀበሉትና እንደማይቀበሉት አላውቅም – ውጤቱን ነገ አያለሁ፤ ዲዲቲና ወባ እንኳን
ተለማምደው ጓደኛሞች መሆናቸውን ቀደም ሲል ሰምተን የለም? የሆነው ሆኖ ችግሩ ቀላል እንዳይመስላችሁ፤ ከአራት ኪሎ
ቤተ መንግሥት የተለቀቁ ነው የሚመስሉት – እንደደፋርነታቸውና እንደሆዳምነታቸው፡፡ የሚምሩት ነገር እኮ የላቸውም፡፡
የሚሆንልኝ መስሎኝ “ዕቃ አትንኩብኝ፤ ቤቱ እንደሆነ ይበቃናል፡፡ ካለኝ አልፎ አልፎ ቀለብ እቆርጥላችኋለሁ –
ከሌለኝ ግን ምን አደርጋለሁ? ብቻ አትተናኮሉኝ እንጂ እኔ መርዝ አላጠምድባችሁም፤ የዛሬን ኑሮ መቼም እናንተም
ታውቁታላችሁ፡፡ ከመጠለቁ እግርን የሚፋጀው እሳተ መለኮቱ የቻይና ካልሲ እንኳን ባቅሙ ሠላሣና ዐርባ ብር በገባበት
ወቅት እባካችሁን ተከባብረን እንኑር፡፡…” ብዬ ቃል ገብቼ በቤቴ ውስጥ የሚያደርሱትን ጉዳት ሰምቼ እንዳልሰማሁና
ዐይቼም እንዳላየሁ ለብዙ ጊዜ ትቻቸው ነበር፡፡ እነሱ ግን የእንጀራ ሞሰብ አልጋችን ላይ አስቀምጠን ከባለቤቴ ጋር
በየተራ እየጠበቅን እስክናድር ድረስ አሰቃዩን – የቤት ውስጥ ወያኔዎች! አሁን ባሰብኝና ቃሌን አፈረስኩ፡፡ እናም …
የነሱስ አብነቱ ቀላል ነው፡፡ አለ እንጂ ወያኔ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ! የወያኔስ ሰማያዊ መርዝ ካልተጨመረበት
በምድራዊ መርዝ ብቻ አይጠራም፡፡ እናም ጎበዝ ግዴላችሁም ለላይኛውም በርትተን እንጩህ፡፡ የቃመ ብቻ ሣይሆን የጮኸም
ተጠቀመ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡
ወያኔና ዐይጥ አንድ ናቸው፡፡ ይሉኝታ አያውቁ፤ ፍቅር አያውቁ፤ ሀፍረትና ኅሊና እሚባል የላቸው፤ የተረገሙ ፀረ-ሕዝቦች፡፡
የሰሞኑ የወያኔ ኢቲቪ ወሬ የአባይ የህዳሴ ግድብ ብቻ ሆኗል፡፡ ነገሩ “አንድ ያላት እንቅልፍ የላት” ዓይነት
ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት በየአሥር ኪሎ ሜትሩ የሚገኝ ግድብ ኢትዮጵያ ውስጥ ብርቅ ሆኖ ጆሯችን እስኪደነቁርና እጅ
እጅ እስኪለን ድረስ አባይን እየተጋትን ነው፡፡ ይህ ግድብ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳው
እንደሚያመዝን ቀድሞውንም የታወቀ ነው፡፡ ፈረንጆቹ አንድን ነገር “politicized” ሆኗል ሲሉ ያ እንዲያ ሆነ
የሚሉት ነገር በፊት ለፊት ከቆመለትና ከሚወራለት ዓላማ ውጪ ለሌላ ጉዳይ ውሏል ማለታቸው ነው፡፡ የወያኔ የህዳሴ
ግድብም ወያኔ እንደሚለው ለሀገሪቱ የሚሰጠው የተለዬ ጥቅም ኖሮ ሣይሆን ሕዝብን ለማዘናጊያነትና ሊጠቀስም ሣይጠቀስ
ሊዘለልም ለሚችል የተለዬ ፖለቲካዊ ፍጆታ መሆኑን እናውቃለን፡፡ አለበለዚያ የስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ኮረንቲ ከቁም
ነገር ተጥፎ እስከዚህን ድረስ 24 ሰዓት ከበሮ የሚያስደልቅና ይቀምሰውና ይልሰው ያጣን ድሃ ሕዝብ ያለ ርህራሄ
የሚያዘርፍ ሆኖ አይደለም፡፡ “አንቺ ቁም ነገርሽ የጎመን ወጥሽ” እንደምንል ወያኔም በዚህች ድልድይ ማነው ግድብ
ዕንቅልፍ አጥቶ እኛንም እንደሱ አትተኙብኝ እያለን ነው፡፡
በማለፊያ ክርስቶሳዊ አባባል አንድ የአደባባይ ምሥጢር እንድናገር መልካም ፈቃዳችሁ ይሁንልኝ፤ “እውነት እውነት
እላችኋለሁ” አባይ ተገድቦ ቢያልቅ በኔም ሆነ በሌሎች ወገኖቼ ሕይወት ላይ አንዳችም ቁሣዊም ሆነ መንፈሣዊ ለውጥ
አያመጣም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ፡፡ እርግጥ ነው – የተሟላ የቴክኒክ ዕውቀት ያለው የሰው ኃይል ካለና እንዳሁኑ
በተጭበረበረ የግዢ ሂደት አማካይነት ፎርጅድና የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሶ የተጣለ የማቴሪያል አቅርቦት ከተወገደ
እንዲሁም የሕዝብ ብዛት በቁጥጥር ሥር ከዋለ ምናልባት ልክ እንዳሁኑ በመብራት ዕጦት ዳፍንት ውስጥ ላንገባ እንችል
ይሆናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ልክ እንዳሁኑ ሁሉ ለማይጠረቃው የመንግሥት ባለሥልጣናት ኪስ ማደለቢያና
ለአነስተኛ የሀገር ገቢ ሲባል ቤት ያለው ሰው ሳይጠግብ ለዬጎረቤት ሀገር ኮረንቲ መቸብቸቡ ከቀጠለ የዚያኔም ቢሆን –
አባይም ተገድቦ ማለት ነው – የመብራት ፈረቃው ላይቀርልን ይችላል፡፡ እናም በአባይ ግድብ ሳቢያ ከወያኔ ጋ ድብን
ያለ ፍቅር የገባችሁ ወገኖች እውነቱን ከወዲሁ እንድትረዱት ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ ወጥመድ ውስጥ ዘው ብላችሁ
አትግቡ፡፡ ሀገር ካላችሁ ሁሉም አለና፡፡
ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖረን አንድ አይደለም አሥርና ከዚያም በላይ ትላልቅ ግድቦች ሊኖሩን የመቻላቸው ዕድል ሰፊ
ነው፡፡ “ልማታዊ መንግሥታችን፤ ባለራዕዩና አባይን የደፈረ ጠቅላይ ሰይጣናችን ማነው ሚኒስትራችን” እያላችሁ ሟቹን
ወያኔ የምታንቆለጳጵሱ ጥቅመኞች ሁሉ ዐይናችሁን ወደጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ አዙሩና እውነቱን ለመረዳት ሞክሩ፡፡
ወያኔ ከኢትዮጵያ ታሪክ አንጻር ዕድሜው የጤዛ ያህል ነው፡፡ በማታለልና በማጭበርበር 23 ዓመታትን መኖሩም የሚገርም
ነው፡፡ ለዚህ ቆይታው ግን ተጠያቂው ወያኔ ብቻ ሣይሆን በተንሸዋረረ ልማት ስም አንጀታቸው ለወያኔ የሚንቦጫቦጭ
አድር ባዮችና እበላ ባይ ሆዳሞች የሚያደርጉለት ሁለገብ እገዛም ጭምር ነው፡፡ የኛም አንድ አለመሆንና በሃሳብ
መለያየት ለወያኔ ዕድሜ መርዘም የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ሌላ ሌላውን ምክንያት እናንተም ታውቃላችሁ፡፡