Friday, December 12, 2014

ባለፈው ዓመት ከሳዑዲ አረቢያ ከተባረሩት ኢትዮጵያውያን መካከል 85ሺው ተመልሰው መሄዳቸው ተዘገበ


ባለፈው ዓመት ከሳውዲ አረብያ ከተባረሩት ከአንድ መቶ ሰባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን 50% (ከ 85ሺህ በላይ የሚሆኑት) ተመልሰው ሳውዲ አረብያ መግባታቸውን አዲስ አበባ ላይ ዛሬ በወጣ አዲስ የዳሰሳ ጥናት ተገለፀ:: (የጉዳያችን አጭር ጥንቅር)

ዛሬ የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበር (CRDA) በሳውዲ ተመላሾች አሁን ያሉበት ጉዳይ ላይ የሚወያይ አውደ ጥናት አዲስ አበባ ላይ የቀረበ አንድ ጥናት ባለፈው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ከተባረሩት ከአንድ መቶ ሰባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን 50% (ከ 85ሺህ በላይ የሚሆኑት) ተመልሰው ሳውዲ አረብያ መግባታቸውን ይገልፃል።ቪኦኤ የአሜሪካ ራድዮ የአማርኛው አገልግሎት ዘጋቢ ከአዲስ አበባ አውደ ጥናቱን አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ የክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ማኅበር (CRDA) የስትራቴጂክ ቡድን መሪ እና በድርጅቱ ልዩ አማካሪ አቶ ክፍለ ማርያም ገ/ወልድን ባነጋገረበት ወቅት ”ሀቁን እንነጋገር ከተባለ ግማሾቹ ተመልሰው ሄደዋል” ብለዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙ የስደት ተመላሾች ውስጥ ለቪኦኤ ሃሳቧን የሰጠች ወጣት ”ከችግር የተነሳ ነው።እዚህ ሆኘ እራሴን ከማጠፋ ሄጄ ልሙት ከማለት ነው” ብላለች።ለወገኖቻችን በአራቱም ማዕዘን መውጣት የሀገራችን አጠቃላይ የፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ከዋና ምክንያትነት አያመልጡም።የችግሩ ዋና መንስኤ እየተተወ ስደቱን ብቻ ብናወጋው መፍትሄ አይሆንም።
የተመላሾቹንም ሆነ የአዲሱን ትውልድ በሀገሩ ተመክቶ እና ተማምኖ እንዲኖር አልተደረገም።ይልቁንም የኢህአዲግ አባል ካልሆነ እና ከካድሬዎች እግር ስር ካለወደቀ መኖር አይችልም።በሥራ ዓለም ያለው ባለሙያንም ብንመለከት የነፃነት ማጣቱ እና ሃሳቡን እና ችሎታውን ለሀገሩ ማበርከት አልቻለም።መሃንዲሱ፣የህክምና ዶክተሩ እና የአይሮፕላን አብራሪው በሀገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ ተደረገ።ሁሉ ሃገሩን ጥሎ ለመሄድ አኮበኮበ የቀረው ቆርጦ ከኢህአዴግ/ወያኔ ጋር ተጋፈጠ።ለእዚህ አብነት የሚሆኑን የሰማያዊ ፓርቲ እና የዘጠኙ አጋሮቻቸው ድርጊት ተጠቃሽ ነው።
የኢትዮጵያ ጉዳይ በእንዲህ አይነት ሁኔታ እንደሀገር የመቀጠላችን አደጋ በራሱ በግልፅ ይታያል።ጥቂቶች በሙስና እና በጎሳቸው ብቻ በሀብት ሲናጥጡ ሌላው ዜጋ ሃገሩን በረሃ ለበረሃ እየተንከራተተ ሲወጣ አይኖርም።አንድ ቀን እዝያው ሀገር ውስጥ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ የመውጣታቸው አደጋ አይኖርም ማለት አይቻልም።የወገኖቻችን ሀገር ጥለው የመሄድ ጉዳይ የሚያመለክተው ይህንን ነው።ቁጥር ደግሞ ከሁሉ በላይ የሀገራችንን የፖለቲካ መድረክ መቀየር እንዳለበት አመላካች ነው።”ከሰማንያ ሺህ በላይ የሚሆኑ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ወገኖቻችን ተመልሰው መከራ ወደ አዩባት ሳውዲ ተመለሱ” የሚለው ዘገባ በእራሱ መጪውን አመላካች ነው።እናት ልጇ ተመልሳ እቤት ከገባች በኃላ ተመልሳ ስትሰደድ እንዴት ታዝን? ምን ያልደረሰብን አለ? ሱዳን ባቅሟ ኢትዮጵያውያንን አባረረች ስንባል፣የመን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መንገዶቿን ሞሉ ሲባል፣ጅቡቲ ኢትዮጵያንን ስታስር፣ እራሳችንን መጠየቅ ያሉብን ሶስት ጥያቄዎች አሉ እነሱም –
ኢትዮጵያ ክብሯ እና ማንነቷ አልተዋረደም ወይ?
ያለውን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየር የፖለቲካው ችግር አለመስተካከል ዋነኛው ምክንያት አይደለም ወይ? እና
ለእዚህም ተጠያቂዎች የእያንዳንዳችን ለስርዓቱ መቀየር የአቅማችንን አለማድረግ አይደለም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች።
በመሆኑም ሰቆቃ ስንሰማ የምንኖርበት ዘመን እንዲቆም፣ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ፣በሙስና የተነከረው እና ክብሯን እና ማንነቷን ከሚመጥናት በታች የሆነ አስተሳስብ ያለው ኢህአዲግ/ወያኔ የበለጠ ሀገራችንን መቀመቅ ሳይከት የእያንዳንዳችንን ኃላፊነት እንወጣ።በዝምታችን ኢትዮጵያን ከሚገድሉ ጋር አንተባበር።

Wednesday, December 10, 2014

የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ መንግሥት ከምዕራብ የፋይናንስ ተቋማት እንዲበደር አሳሰቡ፡፡


  • 200
     
    Share
World-Bankየዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፣ መንግሥት ለካፒታል ፕሮጀክቶች ከአንድ የገንዘብ ምንጭ ብቻ መበደር እንደሌለበትና ይልቁኑም ለምዕራብ የገንዘብ ተቋማት በሩን ክፍት ሊያደርግ እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ ለገሱ፡፡
ሁለቱ ግዙፍ የገንዘብ ተቋማት በኅዳር ወር መጨረሻ ከዋሽንግተን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፣ በርካታ የአውሮፓ ባንኮች የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች ብድር ለመስጠት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን መንግሥት በቂ ድርድር በማድረግ የሚቀርብለትን ፋይናንስ መጠቀም ሲገባው፣ ፈጣን ምላሽ አለመስጠቱንና ከአንድ ምንጭ ብቻ መጠቀሙን (የቻይና መንግሥት) ደብዳቤው ጠቁሞ፣ አንድ የገንዘብ ምንጭ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ ጉዳት እንዳለው ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በአንፃሩ የጀርመን፣ የእስራኤልና የእንግሊዝ ባንኮች ለኢትዮጵያ ፋይናንስ ለማቅረብ ዝግጁ ቢሆኑም የመንግሥትን ትኩረት አለማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡
የሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት ደብዳቤ መንግሥት በቅርቡ ቦንድ ለዓለም ገበያ ማቅረቡን መልካም ጅማሬ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከዚህ በበለጠ ምዕራባዊ ባንኮችን ሊጠቀም እንደሚገባና አንድን የገንዘብ ምንጭ ብቻ መጠቀም ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ይገልጻል፡፡
ክሬዲት ስዊስ፣ በርክሌ፣ ጄፒ ሞርጋንና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የመሳሰሉ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ ለማቅረብ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ሁለቱ የገንዘብ ተቋማት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ግኝቶች ላይ ግምገማ ማካሄዳቸውን ገልጸው፣ የንግድና የካፒታል ፕሮጀክቶች ብድሮች ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ በአንድ የገንዘብ ምንጭ ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸውን በግምገማቸው መረዳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ተቋማቱ መንግሥት የዕዳ አስተዳደሩን መቀየጥ እንደሚኖርበት በጻፉት ደብዳቤ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ መንግሥት ለካፒታል ፕሮጀክት አብዛኛውን ብድር የሚያገኘው ከቻይና መንግሥት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና እየተቸረው በመሆኑ፣ የምዕራብ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ለማቅረብ ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡ ነገር ግን ከቻይና ሲነፃፀር፣ የምዕራብ የፋይናንስ ተቋማት የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ስለሆነ መንግሥት ብዙም ትኩረት እንዳላደረገ ምንጮች ይናገራሉ፡፡