Saturday, May 11, 2013

"ከእኔ ልጅ ጋር ሐረር ከተማ ውስጥ አራት ሰው በፓሊስ ነዳጅ እየተደፋበት በእሳት ተቃጥሎ ሞቷል"



ወ/ሮ ኢትዮጵያ ይልማ (ከሐረር የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸው የተባረሩ አዛውንት)
ፍኖተ ነፃነት (መጋቢት 7 ቀን 2005 ዓ.ም.)፦ "ልጄ በእሳት ተቃጥላ እንድትሞት ተደርጋ፣ ቤቴን ተነጥቄና ንብረቴ ወድሞ ከሐረር ተባረርኩ" ሲሉ አንዲት የ67 አመት ባልቴት በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ አስታወቁ።


ወ/ሮ ኢትዮጵያ ይልማ የሚባሉት እኚሁ እናት የ75 ዓመት አዛውንት የሆኑት ባለቤታቸውም እንደ እሳቸው ሁሉ ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ለፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ዘጋቢ ከዕንባቸው ጋር እየታገሉ አስረድተዋል።

"በሐረር ከተማ ቀበሌ 17 ውስጥ ከ30 ዓመት በላይ ኖሬ፤ ሀብትና ንብረት አድርቼ እኖር ነበር አሁን ግን በአካባቢው እንዳልኖር ተደርጌያለሁ" የሚሉት ወ/ሮ ኢትዮጵያ ይልማ "ከ30 ዓመት በላይ የኖርኩበትን ቤቴን የወረዳው አስተዳዳሪ እና የወረዳው ፓሊስ አዛዥ አስጠርተው ቤትሽን ለወ/ሮ አኒሳ መሐመድ ሸጠሽ ግቢውን እንድታስረክቢያት አሉኝ። እኔ ቤቴን የመሸጥ ሐሳብ የለኝም። ቤቴን ሸጪ የት እወድቃለሁ? አልሸጥም አልኳቸው እንቢ ካልሽ ከአገራችን እናባርራሻለን በገንዘብ አልሸጥም ካልሽ በባዶሽ ተባረሽ ወደ አገርሽ ትሄጃለሽ አሉኝ። እኔ ሌላ አገር የለኝም የምሄድበትም ቦታ የለኝም መንግስት ባለበት አገር ቤትሽን ተቀምተሽ ውጪ የሚለኝ የለም ብዬአቸው ተመለስኩኝ" በማለት የችግሩ መነሻ ነው ያሉትን ጉዳይ ወደኋላ መለስ ብለው ያስረዳሉ።

ጎስቋላዋ የ67 ዓመት ባልቴት በመቀጠልም "በማግስቱ እኔ ቡና አፍልቼ፣ ባለቤቴም ጫማውን አውልቆ ፍራሽ ላይ አረፍ ብሎአል፤ አንድ ፓሊስ በሩን በሰደፍ እና በእርግጫ መቶት በሩን በረገደው። ምንድነው? ብለን ስንወጣ ከ30 በላይ ፓሊሶች ቤታችንን ከበውታል። ይህች ናት። ነይ ውጭ! ብሎ ለሁለት ሶስት ሆነው ጎተቱኝ። እባካችሁ ምን አደረኩ ብዬ ስለምናቸው አንቺ ለህግ አልገዛ ያልሽ አመጸኛ ነሽ! ወንጀለኛ ነሽ እያሉ መሬት ለመሬት ጎተቱኝ። እባካችሁ ምንም የሰራሁት ወንጀል የለም ብዬ ጮኩኝ። ጎረቤት ተሰበሰበ ምንድነው ብሎ ጠየቀ ማንም ምላሽ አልሰጠም" የሚሉት ወ/ሮ ኢትዮጵያ ይልማ ሟች ልጃቸውን በሀዘን ተውጠው እያስታወሱ ይቀጥላሉ "ልጄ ባል አግብታ የምትኖረው ሌላ ቦታ ነው። ቀን ቀን ምግብ እየሰራች ትሸጣለች ፓሊሶች እናትሽን ከበው እየደበደቡ ናቸው ብሎ ጎረቤት ሲደውልላት ሮጣ መጣች። ደርሳ ምን አድርጋ ነው ብላ ብትጠይቅ ቤቱን አስረክቢ ስትባል እንቢ ብላ ነው አሏት። የተወለድንበትና ያደግንበትን ቤት ከህግ ውጭ እንዴት እንነጠቃለን ብላ ስትጮህ ጥላው ሄዱ" በማለት በለቅሶ ያስረዳሉ።

ወ/ሮ ኢትዮጵያ ይልማ በመቀጠልም "ያንለቱኑ ማታ ልጄ ምግብ የምትሸጥበት ቦታ ሁለት ሰዎች ተመጋቢ መስለው ከገቡ በኋላ (ረመዳን የተባለ ፓሊስና እንዳለ ግርማ የተባለ ወጣት) ቤቱን አስረክቡ ስትባሉ አናስረክብም የምትሉት ለምንድነው ብለው ረመዳን ልብሷና ሰውነቷ ላይ ጋዝ ሲደፋባት እንዳለ ግርማ የተባለው ላይተር ለኩሶ አቃጥለዋታል። ሳትሞት ሆስፒታል ደርሳ ነበር። በማግስቱ አዲስ አበባ አምጥቼ ላሳክም መኪና ተከራይቼ ይዤ ስወጣ ፓሊስ እዚህ ትታከም እንጂ ከሐረር አትወጣም ብሎ ከለከለኝ። እኔም ገንዘብ ካለኝ እንኳን አዲስ አበባ አሜርካን ወስጄ ባሳክም ለምን እከለከላለሁ ብዬ ብጮህ ባለቅስ ማንም ሊደርስልኝ አልቻለም። ልጄ ህክምና አጥታ ሞተች።" ብለዋል።

ባልቴቷ ከልጃቸው ሞት በኋላ የደረሰባቸውን በምሬት ያወጋሉ "እኔንም ከቤቴ አስወጥተው ቦታውን ሺጭላት ላሏት ሴት ሰጧት። አሁን ቦታዬ ላይ ፎቅ እየተገነባ ነው። እኔና ባለቤቴ ግን ጎዳና ተጣልን። የአካባቢው ህብረተሰብ አዋጥቶ የሰጠኝን 3ሺ ብር እንድ ፓሊስና አንድ ደላላ መጥተው ነጠቁኝ። ሐረር ውስጥ አደሬ ወይም ኦሮሞ ካልሆንክ አቤት የሚባልበት ቦታ የለም። አማራ ነው ከተባለ ሁሉም ባለስልጣን በደረሰበት ግፍና ስቃይ ይስቅበታል። በደርግ ጊዜ የሐረር ፓሊስ አዛዥ ትግሬ ነበር፤ የማረሚያ ቤት አዛዥም ትግሬ ነው። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ትግሬ ነው። ለምን ትግሬ ሆነ ያለ አንድም ሰው የለም። ዛሬ በሐረር በየትኛውም መስሪያ ቤት አማራ ባለስልጣን የለም። ባለቤቴ ኦሮሞ ነው። ልጆቼም ኦሮሞ ናቸው። እኔ አማራ በመሆኔ ብቻ ይህ ሁሉ ጉዳት ተፈጸመብን።" የሚሉ ወይዘሮዋ የተፈፀመባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘራቸውን መሰረት ያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።

አክለውም "አዲስ አበባ መጥቼ ለእንባ ጠባቃ ተቋም አመለከትኩኝ። ፌደራል እንባ ጠባቂ ተቋም እንዴት እንዲህ ይፈጸማል ብለው ይዘውኝ ሐረር ተመለሱ። የቤቴ ካሳ እንዲከፈለኝ ተወሰነልኝ። የክልሉ ባለስልጣናትም እሺ ይፈጸምሎታል ብለው ቃል ገቡልኝ። እንባ ጠባቂዎቹ ወደ አዲስ አበባ ተመልሱ። እነሱ ከተመለሱ በኋላ ግን ምንም መፍትሄ አልሰጡኝም። በድጋሚ አዲስ አበባ መጥቼ ለእንባ ጠባቂ ተቋም ባመለክት እነሱም ውሳኔያቸውን እንደ አጀማመራቸው ሊያስፈጽሙልኝ አልቻሉም። ጉዳዬንም ለመስማት ፍቃደኛ አልሆኑም።" በማለት የበደላቸውን ስፋት ለፍኖተ ነፃነት ዘጋቢ በዝርዝር አስረድተዋል።

"ዛሬ እኔ አዲስ አበባ ላይ ባለቤቴ ደግሞ ሐረር ላይ ጎዳና ላይ ነን። መፍትሔ ማግኘት አልቻልኩም" ሲሉ ተስፋ መቁረጥና ምሬት ተሞልተው በለቅሶ የመንግስት ያለህ ... የህዝብ ያለህ በማለት ጥያቸውን ያቀርባሉ።

የወ/ሮ ኢትዮጵያ ይልማን ጉዳይ አስመልክቶ የፌደራሉ እንባ ጠባቂ ተቋም ለሐረሪ ክልላዊ መንግስት ጸጥታ ቢሮ የጻፈውን ደብዳቤ እንደተመለከትነው ደብዳቤው ከዚህ በፊት ስለጉዳዩ ተጠይቆ መልስ አለመስጠቱን በማስታወስ አሁን በድጋሚ በ 15 ቀን ውስጥ መልስ እንዲሰጥ ያለበለዚያ በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የሚገልጽ ነው። ሆኖም የእምባ ጠባቂ ተቋም ውሳኔ ባልቴቷንና ባለቤታቸውን ከጎዳና ተዳዳሪነት የሚታደግ አልሆነም።

በጉዳዩ ላይ የፊደራል እንባ ጠባቂ ተቋም አስተያየት እንዲሰጥበት ወደ ተቋሙ ህዝብ ግንኙነት ክፍል በማምረት ባለሙያዎችንም አነጋግረን ነበር። በቅድሚያ ያነጋገርናቸው የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ ጉዳዩን ከስሙንና በእጃችን ያለውን መረጃ ከተመለከቱ በኃላ ወደ ሌላው የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያ ማስረጃችንን ከተመለከቱ በኃላ ይህንን ጉዳይ የሚያውቁት ዋና አማካሪው አቶ ቀነአ ሶና ናቸው፡፤ እሳቸውን አነጋግሩ አሉን። አቶ ቀነአን በወቅቱ ማግኘት አላቻልንም። በሌላ ጊዜ ተመልሰን ቢሮአቸው ያሉትን የተቋሙን ሰራተኛ አቶ ቀነአን እንደምንፈልግ አስረዳናቸው፤ አቶ ቀነአን ወደ መስክ ወጥተዋል። ሰሞኑን ቢሮ አይገቡም አሉን። በዚህ ምክንያት የፌደራሉን እንባ ጠባቂ ተቋም አስተያየት ማካተት አልቻልንም።

ጉዳዩ ተከቷል ወደ ተባለለት ወረዳ ፖሊስ ደወልን የሐኪም ወረዳ ፖሊስ ወንጀል መከላከል ሀላፊ የሆኑትን ሳጂን ተሾመ ሰይፉን አግኝተናቸዋል። ወ/ሮ ኢትዮጵያ ይልማ ደረሰብኝ የሚሉትን በደል ወቅቱን ጠቅሰንም አስረድተናቸዋል። ሆኖም ሳጂን ተሾመ ሲመልሱ "እኛ ፖሊሶች በየሁለት ዓመቱ እንቀያየራለን። አሁን በዚህ ወረዳ ያለነው ከሁለት ዓመት ወዲህ ተዛውረን የመጣን ነን። ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቅ ሰው የለም። በአሁኑ ወቅት በወረዳችን መሩን።እሳቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ ሮመዳን የሚባል ፖሊስ የለም። ምናልባት የወረዳው መስተዳድር የሚያውቁት ነገር ካለ እነሱን ብትጠይቁ ይላል።" በማለት መልሰውልናል።

በአሁኑ ጊዜ ያሉትን የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ኢስማኤልንም ስለጉዳዩ ጠይቀን በሰጡን መልስ "እኔ በቅርብ ጊዜ ነው የመጣሁት ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም። የሚያውቁት ነገር ካለ ከእኔ በፊት የነበሩትን ጠይቋቸው" ብለውናል። ከእሳቸው በፊት የወረዳው አስተዳዳሪ የነበሩትን አቶ ጀማል አህመድን አፈላልገን ጠየቅናቸው። "እኔ ድርጊቱ ተፈፀመ በምትለኝ ወቅት እዚያ ወረዳ አልሄድኩም። ስለዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም። ከእኔ በፊት የነበረውን ሰው አፈላልጋችሁ ጠይቁ ብለውናል።" ከእሳቸው በፊት የነበሩትን አስተዳዳሪ ማንነትና አድራሻ ማግኘት ባለመቻላችን ዜናውን በተገቢው ሁኔታ ሚዛናዊ ማድረግ አልቻልንም።
(ሙሉውን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

Friday, May 10, 2013

ሲጠበቅ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በደቡብ አፍሪካ ዛሬ ተካሄደ

http://ecadforum.com/Amharic/archives/7684

ሲጠበቅ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በደቡብ አፍሪካ ዛሬ ተካሄደ

ክራንቻ፣ ከደቡብ አፍሪካ
በዛሬው ዕለት የተደረገውን ሰልፍ ለማደናቀፍ የወያኔ መንግስት ጭፍሮች ለዲፕሎማቶች እና ለፖሊስ የሰጡት የሀሰት ውንጀላ በትላንትናው ዕለት ውድቅ ተደርጎ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ የሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል።
ተቃዋሚ ሀይሎች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሰለፍ እጅግ የፈራው ወያኔ ሰልፉን የጠሩት አሸባሪዎች ናቸው፣ ከዚህ በፊትም ቴዎድሮስ የሚባለውን የኢትዮጵያ ባለስልጣን በደርባን ርዕሰ ከተማ የጠለፋ ሙከራ ሊያካሂዱበት ነበር የሚልና መሰል የሀሰት ውንጀላዎችን በመደርደር ቢሟገትም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የደቡብ አፍሪካን ዲሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት የሚጻረር ስህተት ላለመፈጸም ሲል የሰላማዊ ሰልፉን ፈቃድ በደቡብ አፍሪካ ነዋሪ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ሰጥቷል።
በመሆኑን ዛሬ አርብ ሜይ 10፣ 2013 ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በጆሀንስበርግ የተሰበሰበው ህዝብ ወደ ፕሪቶሪያ ጉዞውን በማድረግ የስብሰባው ስፍራ ተገኝቶ መልዕክቱን በቃልና በደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ልዑክ እና ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ቃል-አቀባይ፣ በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካይ አቶ ደረጀ አማካኝነት አስረክቧል።
ሌላው በሰላማዊ ሰልፉ ወቅት የተፈጠረ አስገራሚ ነገር ቢኖር፣ የኦጋዴን ተቃዋሚ ሀይሎች በስፍራው በመገኘት “ከወያኔ እንጂ ከኢትዮጵያ ህዝብ የመገንጠል ሀሳብ የለብንም… ወያኔ ይወገድ!” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከ ኦጋዴን ወገኖቻችን መካከል አንዲት እህታችን ይዛ የነበረው መፈክር የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነበር። እንዲህ ይነበባል፣

“60% OF ETHIOPIAN GPD IS WESTERN AID TO KILL CIVILIANS”

ድል ለሰፊው ህዝብ!

Thursday, May 9, 2013

ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ለከት የለው፤ የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው፡፡

http://addisdibab.wordpress.com/2013/05/07/letter-from-reeyot/

ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ለከት የለው፤
የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው፡፡

የቃሊቲው ደብዳቤና የርዕዮት እውነቶች
በስለሺ ሀጎስ
ሚያዝያ 23 2005 ዓ.ም ሪፖርተር ጋዜጣ በቅጽ 18 ቁጥር 44/1356 ዕትሙ “በህግ ታራሚ ርዕዮት ዓለሙ ላይ የደረሰ አንዳችም አይነት ችግር የለም!” በሚል ርዕስ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የተላከ ደብዳቤ አስነብቧል፡፡ ደብዳቤው በቅጥፈትና በክህደት የተሞላ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ባልተነሳ ጥያቄና ባልተባለ ነገር ላይ በማተት የተነሳበትን ሀቀኛ ጥያቄ አደናብሮ ለማለፍ ከአንድ ህገ መንግስታዊ ተቋም የማይጠበቅ ጥረት አድርጓል፡፡
ይህ የሆነውም ርዕዮት ራሷን በማትከላከልበት ሁኔታ ውስጥ መሆኗን እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት ይመስላል፡፡ በመሆኑም በደብዳቤው ላይ የሰፈሩትን አብዛኞቹን ጉዳዮች በቅርብ ስለማውቃቸው የርዕዮትን እውነቶች የማስረዳት ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለብኝ በማመኔ ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ፡፡
በደብዳቤው ከታጨቁ ቅጥፈቶችና ማወናበዶች መሐከል ጸሐፊውን ጠልፈው የሚጥሉ እውነቶች ተሸሽገው ቀርበዋል፡፡ ከነዚህም መሐከል አንደኛው ርዕዮት ለብቻዋ እንድትታሰርና በጠያቂዎቿ እንዳትጎበኝ ለማድረግ ማረሚያ ቤቱ እንደተዘጋጀ ማረጋገጡ ነው፡፡ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ፣
‹‹በማረሚያ ቤት አብረዋት ከሚኖሩ ታራሚዎች ለመረዳት እንደቻልነው ርዕዮት ያለምንም ጥረትና ልፋት ዝናን ለማግኘት በመሻቷ ከታራሚዎችና ከጥበቃ አባሎች ጋር በየጊዜው ትጋጫለች፡፡ ጤናማ የሆነ ግንኙነት የላትም፡፡ በተለያየ ጊዜ በታራሚዋ ላይ የዲሲፒሊን ግድፈት በመታየቱም ማረሚያ ቤቱ ጥፋቱን በማጣራት ላይ ይገኛል፡፡ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘችም በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕግ ታራሚዎች መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 138/1999 መሠረት ተገቢውን የዲሲፒሊን እርምጃ ተቋሙ እንደሚወስድ ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡››
የሚል ሀሳብ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
በጽሑፉ ላይ እንደሚታየው ርዕዮት የዲሲፒሊን ግድፈት ማሳየቷን ማረሚያ ቤቱ ደምድሟል፡፡ ከዚህም በላይ ከጥበቃ አባሎችና ከታራሚዎች ጋር እየተጋጨች የዲሲፒሊን ግድፈቱን የምትፈጽመው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “ያለምንም ጥረትና ልፋት ዝናን ለማግኘት በመሻቷ ከታራሚዎችና ከጥበቃ አባሎች ጋር በየጊዜው ትጋጫለች፡፡ ጤናማ የሆነ ግንኙነት የላትም፡፡” በማለት በልቧ ምን አስባ ድርጊቱን እንደምትፈጽም ሁሉ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ ነግሮናል፡፡
ታዲያ ማረሚያ ቤቱ የሚያጣራው ምንድን ነው? ጥፋተኝነቷን ከነ መንስዔው እርግጠኛ ሆኖ እየነገረን፤ መልሶ ደግሞ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ አልሞ ለመተኮስ ሳይሆን፣ የሚፈልገው ላይ ተኩሶ ዒላማ ለማክበብ መዘጋጀቱን ያሳብቃል፡፡
አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት፣
እያደር ይፈጃል እንደእግር እሳት! ሆነበት እንጂ ነገሩ፡፡
ማረሚያ ቤቱ ከሳሽም፤ አጣሪም፤ ፈራጅም፤ እርምጃ ወሳጅም ሆኖ መቅረቡ ደግሞ “በህግ ሽፋን ርዕዮት ብቻዋን እንድትታሰርና ጠያቂዎቿ እንዳይጎበኟት ለማድረግ እየሰራ ነው” የሚለው ስጋት እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሲፒጄም ቢሆን ያለው ይህንኑ ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደብዳቤው ላይ፤
“በአንዳንድ ሚዲያዎች የተገለጸው ሌላው ጉዳይ ለሁለት ወራት በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻዋ እንደታሰረች የሚገልጸው ዘገባ ነው፡፡ ይህ ዘገባ ከርዕዮት ጋር የሚኖሩ የህግ ታራሚዎችን ከመናቅ ወይም እንደሰው ካለመቁጠር የመነጨ ይመስለናል፡፡ ሀሳቡ የርዕዮት ከሆነም ለራሷ ካላት የተጋነነ ግምት ወይም ማንነት የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡”
የሚል ውንጀላ ቀርቧል፡፡
እግዜር ያሳያችሁ! “ሊሆን ይችላል” ነው ያለው፡፡ ግምት ብቻ ተይዞ “ለራሷ ካላት የተጋነነ ግምት… እንደሰው ካለመቁጠር የመነጨ” የመሳሰሉ ሥነልቡናዊ ትንታኔዎች ውስጥ እንዴት ይገባል? ኧረ ጎበዝ አታሳፍሩን!
እርግጥ ነው ርዕዮት ለብቻዋ እንድትታሰር ሊያደርጋት በሚችል አንቀጽ (በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የሕግ ታራሚዎች መተዳደሪያ ደንብ ቁጥር 138/1999) ክስ ተመስርቶባት ውሳኔውን (ውሳኔው ተግባራዊ የሚሆንበትን ዕለት) በመጠባበቅ ላይ ናት እንጂ በአሁኑ ሰዓት ለብቻዋ አልታሰረችም፡፡
ለዚህ ጉዳይ ሽፋን ከሰጡ በርካታ የሀገር ውስጥ የህትመት ውጤቶች መሐከል አንዱ (ሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 18 ቁጥር 42/1352) ‹‹ርዕዮት ለብቻዋ ታስራ ትገኛለች›› ብሎ ሲፒጄ መናገሩን ጽፏል፡፡ ማረሚያ ቤቱን ለግምታዊ ስህተት የዳረገውም ይሄው ዘገባ ነው፡፡ ነገር ግን እንኳን አንድ ትልቅ ተቋም ቀርቶ፤ የዘገባው ስህተት ከምን የመነጨ እንደሆነ ማረጋገጥ የሚፈልግ ሰው የሲፒጄን ኦርጂናል መግለጫ ማንበብ፤ አሊያም ጋዜጣውን መጠየቅ ብቻ ይበቃዋል፡፡
እኔ ያነበብኩትና ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በአድራሻው የተላከት የሲፒጄ ደብዳቤ “ርዕዮት ለብቻዋ ታስራለች” አይልም፡፡ በጉዳዩ ላይ መረጃ የሰጡ የርዕዮት ቤተሰቦችም በአንድም ሚዲያ ላይ ይህን አላሉም፡፡ ታዲያ ሪፖርተር ከየት አመጣው? የሚለውን ጥያቄም ከጋዜጣው በስተቀር ርዕዮትም ሆነች ማንም ሰው ሊመልሰው አይችልም፡፡
ከዚህ ሌላ ርዕዮት ማረሚያ ቤቱ እንዳለው አይነት ሰው አለመሆኗን ዓለም የሚያውቀው እውነት በመሆኑ ይህን ለማስረዳት አንዲትም ቃል ሳላባክን ወደ ቀጣዩ ርዕሰ ጉዳይ ልለፍ፡፡
ህክምናዋን በተመለከተም ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማት በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡ “ማረሚያ ቤት በቆየችባቸው ጊዜያት በተለያዩ ቀናት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተልካ ሕክምና ማግኘቷን ከግል ማህደሯ ማረጋገጥ ይቻላል” በማለትም እማኝ ይጠቅሳል፡፡
በተለያዩ ቀናት፣ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሄዷ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በጡቷ ላይ ሕመም እንደሚሰማት ተናግራ ሪፈር እንዲጻፍላት ብትጠይቅም፣ ከመንፈስ ጭንቀት ውጪ ምንም በሽታ እንደሌለባትና የእጅ ሥራ እንድትሰራ፤ ጥልፍ እንድትጠልፍ ስትመከር መሰንበቷ፤ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሄዳ ህክምናዋን ለመከታተል የቻለችውም ከብዙ አቤቱታ በኋላ ኦማር የተባለ የአፍሪካ ጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ተወካይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ጋር ቃሊቲ ድረስ ሄደው በጎበኟት ወቅት በእነሱ በኩል በቀረበ አቤቱታ በማረሚያ ቤቱ ዋና አስተዳዳሪ ትዕዛዝ መሆኑ ቢታከልበት የተሻለ እውነት ይሆን ነበር፡፡
ሕክምናዋን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መከታተል ከጀመረች ወዲህም ብዙውን ጊዜ በቀጠሮዋ መሠረት ተገኝታ መታከም አለመቻሏ፤ ህመሟ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ የተለየ ህመም ካጋጠማት ቀጠሮዋን ሳትጠብቅ ወደ ሆስፒታል እንድትመጣ በሀኪሞቹ ቢታዘዝም፤ ከጥር 10 ቀን ጀምሮ ክፍተኛ ደም ከጡቷ እየፈሰሰ እስከ የካቲት 07 ድረስ ህክምና ሳታገኝ በስቃይ መክረሟ፤ ከዚያ በኋላም ሀኪሟ በአስቸኳይ የናሙና ምርመራ ተደርጎ የዕጢው ደረጃ ከታወቀ በኋላ መለስተኛ ቀዶ ጥገና ማድረግ እንደሚኖርባት በመግለጽ ለየካቲት 13 ቀጠሮ ቢሰጥም መኪና የለም በሚል ሰንካላ ሰበብ እስከ መጋቢት 2 ድረስ፣ ከነስቃይዋ እንድትቆይ መደረጓና ሌሎች ታራሚዎች ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቀጠሯቸው ቀን ከፍርድቤትና ከሌሎች ቀጠሮዎች ጋር እንዳይጋጭ የህክምና ቀጠሯቸውን እዚያው ሆስፒታል እያሉ እንዲያውቁት የሚደረግበት አሰራር የተለመደ ሆኖ እያለ ርዕዮት ከመጋቢት 2 ወዲህ መቼ ምን አይነት የሀኪም ቀጠሮ እንዳላት ለማወቅ ብትጠይቅም፣ በግልጽ ‹‹ለአንቺ አይነገርሽም›› መባሏ ተገልጾ ቢሆን ኖሮ ሙሉ እውነት ይሆን ነበር፡፡
ፍጹም እውነት እንዲሆን ደግሞ…
እንጂማ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መሄዷ ብቻ ሳይሆን መለስተኛ ቀዶ ጥገና አድርጋ ከጡቷ ላይ ዕጢ ማስወጣቷም ጭምር ከወራት በፊት ሁሉም የሰማውና ያረጀ ዜና ነው፡፡
የትምህርቷን ጉዳይ በተመለከተ ከመነሻው ጀምሮ እስከ ክልከላው ድረስ እኔ ራሴ ስከታተለው የነበረ በመሆኑ፣ ማረሚያ ቤቱ ላከ በተባለው ደብዳቤ ላይ ያነበብኩት ነገር ክፉኛ አስደንግጦኛል፡፡ ጸሐፊው ትክክለኛ መረጃ ሳያገኝ በየዋህነት ተሳስቶ ካልሆነ በቀር እንዲህ አይነት አይን ያወጣ ቅጥፈት በአደባባይ እንዲነበብ ለመጻፍ በገዛ ህሊናው ላይ የሰለጠነ ልዕለ ኃያል ሰው መሆን ይጠይቃል፡፡
የሆነው ሆኖ “ትምህርቷን እንድትከታተል የሴቶች ቀጠሮና ማረፊያ ቤት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገላት ይገኛል፡፡” ተብሎ የተገለጸው ፍጹም ሀሰት ሲሆን እውነቱ የሚከተለው ነው፡፡
የማረሚያ ቤቱን ይሁንታ ጠይቃ ካገኘች በኋላ ህዳር 29 2012 እ.ኤ.አ ያስመዘገብኳት እኔው ራሴ ነበርኩ፡፡ መመዝገቧን ካሳወቀች በኋላም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የማረሚያ ቤቱ ባልደረቦች ት/ቤቱ ድረስ በመሄድ እንዳረጋገጡ የሰማሁት ከራሳቸው አንደበት ነው፡፡ በየካቲት ወር መጨረሻ ትምህርቱ ሲጀመር የመማሪያ መጻህፍቶቿን ይዤ በሄድኩበት ጊዜ ግን የተሰጠኝ “እሷ እንድትማር አልተፈቀደላትም” የሚል ምላሽ ነው፡፡ ጉዳዩ እስካሁን ድረስ እልባት ባለማግኘቱ ትምህርቷን መጀመር አልቻለችም፡፡ የመማሪያ መጻሕፍቱም እስከ ዛሬ ድረስ በእጄ ይገኛሉ፡፡
በመጨረሻም መሽቶ በነጋ ቁጥር በሁሉም መስክ የባሰ ነገር መጋፈጥ ልማዳችን ነውና ለማረሚያ ቤቱ ደብዳቤ ይህን ያህል ጊዜና ጉልበት ከፈጀን በቂ ነው፡፡ ነገ ለሚመጣው የባሰ ነገር ጊዜና ጉልበት መቆጠብ፣
ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ለከት የለው፤
የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው፡፡
የሚል ቁዘማ ውስጥ ከመዘፈቅ ሳያድነን አይቀርም፡፡
ቺርስ!!




ያምናን ቀን አማሁት ላፌ ለከት የለው፤ የዘንድሮው መጣ እጅ እግር የሌለው፡፡