“
… ወታደር ባለመሆኔ የጦርነቱን ውሎ ማተት አያምርብኝም፡፡ ያም ሆኖ የአድዋ ድል ዛሬ ብርቅ በሆኑብን ሁለት
እሴቶች ረድኤት የተገኘ ይመስለኛል፡፡ እኒህ ሁለት እሴቶች መተባበርና መደማመጥ ናቸው፡፡ ጣልያኖቹ በጊዜው ወደ
ጦርነት ሲገቡ ተስፋቸውን የጣሉት በመድፍና በጠመንጃቸው ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዝነኛ በነበሩበት የውስጥ መቆራቆስ
ላይ ነው፡፡ የትግራይ ቅልጥም ሲመታ ሸዋ ያነክሳል ብለው አላሰቡም፡፡ በርግጥም በክፍለ ሀገሮች ውስጥ የተለያዩ
ሽኩቻዎች ነበሩ፡፡ እኒህን ሽኩቻዎች አስረስቶ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ለአንድ አላማ ማሠለፍ ምኒልክነትን ይጠይቃል፡፡
“መደማመጥ ያልሁትን ላሳይ፡፡ አባ ዳኘው ከዛሬው የይስሙላ ፓርላማችን በተሻለ ሁኔታ ለልዩነቶች ቦታ የሚሰጥ ተንቀሳቃሽ ምክር ቤት በጦርነቱ ወቅት መፍጠር ችለዋል፡፡ ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረሥላሴ በውጊያው ዋዜማ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልፁታል
‘… አፄ ሚኒልክም በበነጋው ሰራዊቱን የቀኙን በቀኝ፣ የግራውን በግራ አሰልፈው ነጋሪትዋን እያስመቱ ወደሱ ተጓዙ፡፡ ኢጣሊያኖችም ዘበኛው ሲመጣ ባዩ ጊዜ ተመልሰው ወደ እርዳቸው ገብተው ተኙ፡፡
ከዚህ በኋላ ሰራዊቱም እንደ ኤሊ ስንመጣበት ከድንጋይ ይገባል፤ ስንመለስ ይወጣል፤ እንዲህ አርጐ ሊጫወትብን ነውን? ብሎ እጅግ አጥብቆ ተናደደ፡፡ መኳንንቶቹም ተሰብስበው ከዚህ ሰፍረን አድረን በማለዳ እዚያው ካሉበት ከርዱ ድረስ ሄደን እንዋጋለን ብለው መከሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም እሺ ብለው ድንኳኑን ለማስመጣት አዘዙ፡፡
ይህ ምክር ካለቀ በኋላ የትግሬው ገዢ ራስ መንገሻ ተሰልፎ በፈረስ ሆኖ መጣ፡፡ እሱም ይህ ምክር እንዳለቀ ባዬ ጊዜ አንድ ነገር ልናገር ይፍቀዱልኝ ብሎ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ እንዲህ አለ፡፡ እንደ ተርታ ነገር ካልሆነ ስፍራ ሄደን ልናስፈጀው ነውን? አለ፡፡ ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክም ተመልሰው ከድንኳንዋ ከገቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡፡ እንግዲህ ከሰፈሬ ወጥቶ ተኩስ አልጀመረ ባይኔ ካላየሁት ተሰልፌ አልወጣም፡፡’
“ፀሐፌ ትእዛዝ ያቀረቡትን ዘገባ ወደ ዘመናዊ አማርኛ አሳጥሬ ሳዛውረው የሚከተለውን ይመስላል፡፡
“ርዕሰ-ብሔር ምኒልክ ሰራዊታቸውን እየመሩ ወደፊት ሲገሰግሱ የጣልያን ሰራዊት ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ ወደ ምሽጉ ገባ፡፡ ምኒልክ በቀጣዩ ስትራቴጂ ላይ ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ፡፡ በስብሰባው ላይ ወደ ጠላት ምሽግ ሄደን እንዋጋ የሚል ሐሳብ ቀርቦ ባብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡ ምኒልክም በብዙሃኑ ተሰብሳቢ የቀረበውን ሐሳብ ለማስፈፀም ተዘጋጁ፡፡ ይሁን እንጂ ጄኔራል መንገሻ ዮሐንስ ዘግይቶ ስብሰባውን ከተቀላቀለ በኋላ “ምሽግ ድረስ ሄዶ መዋጋት በወገን ጦር ላይ ጉዳት ያስከትላል” ብሎ መከራከር ጀመረ፡፡ ምኒልክም “እኔ አንዴ ወስኛለሁ፤ ውሳኔዬ ካልጣመህ በሊማሊሞ በኩል ማቋረጥ ትችላለህ” ብለው ሳያሸማቅቁት ሐሳቡ እንዲጤን አደረጉለት፡፡ ሐሳቡ በድምፅ ብልጫ ፀደቀ፡፡ በድምፅ ብልጫ ያልሁት “ይህ ምክር የተስማማ ምክር ሆነ” የሚለውን የፅሐፌ ትዕዛዙን አማርኛ ተርጉሜ ነው፡፡”