Wednesday, December 10, 2014

የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ መንግሥት ከምዕራብ የፋይናንስ ተቋማት እንዲበደር አሳሰቡ፡፡


  • 200
     
    Share
World-Bankየዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፣ መንግሥት ለካፒታል ፕሮጀክቶች ከአንድ የገንዘብ ምንጭ ብቻ መበደር እንደሌለበትና ይልቁኑም ለምዕራብ የገንዘብ ተቋማት በሩን ክፍት ሊያደርግ እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ ለገሱ፡፡
ሁለቱ ግዙፍ የገንዘብ ተቋማት በኅዳር ወር መጨረሻ ከዋሽንግተን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በጋራ በጻፉት ደብዳቤ፣ በርካታ የአውሮፓ ባንኮች የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያካሂዳቸው ፕሮጀክቶች ብድር ለመስጠት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን መንግሥት በቂ ድርድር በማድረግ የሚቀርብለትን ፋይናንስ መጠቀም ሲገባው፣ ፈጣን ምላሽ አለመስጠቱንና ከአንድ ምንጭ ብቻ መጠቀሙን (የቻይና መንግሥት) ደብዳቤው ጠቁሞ፣ አንድ የገንዘብ ምንጭ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ ጉዳት እንዳለው ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡
በአንፃሩ የጀርመን፣ የእስራኤልና የእንግሊዝ ባንኮች ለኢትዮጵያ ፋይናንስ ለማቅረብ ዝግጁ ቢሆኑም የመንግሥትን ትኩረት አለማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡
የሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት ደብዳቤ መንግሥት በቅርቡ ቦንድ ለዓለም ገበያ ማቅረቡን መልካም ጅማሬ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከዚህ በበለጠ ምዕራባዊ ባንኮችን ሊጠቀም እንደሚገባና አንድን የገንዘብ ምንጭ ብቻ መጠቀም ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል ይገልጻል፡፡
ክሬዲት ስዊስ፣ በርክሌ፣ ጄፒ ሞርጋንና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የመሳሰሉ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ መንግሥት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ ለማቅረብ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ሁለቱ የገንዘብ ተቋማት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ግኝቶች ላይ ግምገማ ማካሄዳቸውን ገልጸው፣ የንግድና የካፒታል ፕሮጀክቶች ብድሮች ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ በአንድ የገንዘብ ምንጭ ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸውን በግምገማቸው መረዳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ተቋማቱ መንግሥት የዕዳ አስተዳደሩን መቀየጥ እንደሚኖርበት በጻፉት ደብዳቤ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ መንግሥት ለካፒታል ፕሮጀክት አብዛኛውን ብድር የሚያገኘው ከቻይና መንግሥት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና እየተቸረው በመሆኑ፣ የምዕራብ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ለማቅረብ ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡ ነገር ግን ከቻይና ሲነፃፀር፣ የምዕራብ የፋይናንስ ተቋማት የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ስለሆነ መንግሥት ብዙም ትኩረት እንዳላደረገ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

No comments:

Post a Comment